News and Updates News and Updates

የመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክና ረቂቅ ፖሊሲና አዋጅ ላይ ውይይት ተደረገ

የግሉ ዘርፍ በሀገራችን ኢኮኖሚ  የሚኖረውን ድርሻ ያሳድጋል የተባለው የመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክና (Public-Private Partnership) ረቂቅ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ላይ ከመንግስት እና ከግል ዘርፍ ባለደርሻ አካላት ጋር ከየካቲት 16- 17 / 2009 ዓ.ም. ውይይት ተደረገ፡፡

በውይይቱ ወቅት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንደተናገሩት በአገራችን ላለፋት አስራ አምስት ዓመታት በተከታታይ ለተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት መንግስት ለመሰረተ ልማት የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ቁልፍ ሚና መጫወቱን ገልፀው የመሰረተ ልማት ጉድለትን ለመሸፈን መንግስት ትልቅ ፋይናንስ ሲመድብ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም የኢኮኖሚውን ዕድገትና ተወዳዳሪነት ይበልጥ ከፍ ለማድረግ በቀጣይ ጊዜያትም ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት በመሠረተ ልማት ላይ በማዋል መሥራት የሚያስፈልግ ቢሆንም መንግሥት ለመሠረተ ልማት የሚውል ፋይናንስ ለማቅረብ ያለው አቅም ውስን እየሆነ መሄዱ የማይቀር ስለሆነ በዚህ ረገድ የግል ፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ዕውቀት ይበልጥ ለመጠቀም የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

በዚህም መሰረት በኢትዮጲያ የመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክና የሚመራባቸውን ፖሊሲዎችና ህጎች ረቂቅ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመከረበት ይገኛል፡፡ ረቂቅ ፖሊሲው አንዳሚያስረዳው መንግስታት የመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክናን የሚያራምዱት ለልማት የሚያስፈልግ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳደግ አንዲሁም ቅልጥፍናና ፈጠራን ለማራመድ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ሀገራት አንደታየው የመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክና የልማት ፕሮጀክቶች በታቀደው በጀትና ጊዜ አንዲጠናቀቁ፣ የተሻለ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አስተዳደር አንዲኖር አንዲሁም ለወጣበት ወጪ ተመጣጣኝ ዋጋ የሚያስገኝ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጨማሪ ጉልበት ከመሆኑም በላይ የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ደርሻ እንደሚያሳድገው ጠቅሰው ረቂቅ አዋጁ በመንግስትና የግል ዘርፍ ሽርክና ተሳታፊዎች ዕኩል የሆነ መብት አንዲኖራቸው፣ ስራውን የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት አንዲሁም ሊገጥሙ ስለሚችሉ ስጋቶች መንግስታዊ ዋስትና አንደሚያስፈልገው እንዲሁም ስራውን ሰለሚመራው ቦርድ የተሰጡ አስተያየቶች ረቂቅ ፖሊሲውንና አዋጁን ለማሻሻል አንደሚጠቅሙ  ተገልጧል፡፡