News and Updates News and Updates

የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማረጋገጥ የመንግስት ልማት ድርጅቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተገለፀ

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዘጋጅነት የካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደውን የውጭ ሀብት አስተዳደርና የመንግስት የልማት ድርጅቶች የገቢ አስተዳደር የምክክር መድረክን በንግግር የከፈቱት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እንደገለጹት የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ የአገር ውስጥና የውጪ ብድር አስተዳደር ስርዓትን በተመለከተ ግልጽነትና መተማመን በመፍጠር የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ በማረጋገጥ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከያዙት ትላልቅ ፕሮጀክቶችና በጀት አንጻር ከመንግስት ጋር በመሆን የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ትልቁን ድርሻ እንደሚጫወቱም ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል፡፡

ከመደበኛው የመንግስት የወጪ በጀት 80 በመቶ ያህሉ የሚሸፈነው ከአገር ውስጥ ገቢ ሲሆን ቀሪው 20 በመቶው ደግሞ ከውጭ ከሚገኘው ብድርና እርዳታ እንደሆነ& ከብድር እና እርዳታ የሚገኘው ሀብትም ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ላይ እንዲውል ቢደረግም  አሁንም ድረስ በፋይናስ ስርዓታችን ላይ ድክመቶች እንዳሉ የማይካድ ሃቅ እንደሆነ በመድረኩ ተገልጽዋል፡፡

የልማት ድርጅቶች በአገሪትዋ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ቢሆንም የብድር አቅርቦት ፍላጎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነም ተወስቷል፡፡ "የልማት እቅዱንና ኢንቨስትመንቱን በተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ማስቀጠል የምንችለው ድርጅቶቹ ትርፍና ገቢ ማምጣት ሲችሉ ነው በማለት ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ ይህንን ለማረጋጥ ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱ የምክክር መድረክ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ብለዋል፡፡

የልማት ድርጅቶች ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከሆኑ ተመሳሳይ የምክክር መድረክ በየስድስት ወሩ ቢካሄድ እንዲሁም ወደኋላ የቀሩት ፕሮጀክቶች ማንሰራሪያ መንገድ ቢበጅላቸው ጉዳዮ ወቅታዊ እንደመሆኑ መጠን ድርጅቶች ካለፈው ስህተታቸው ልምድ በመውሰድ አስፈላጊውን ማሻሻል ማሳየት ይችላሉ የሚል አስተያየቶች በውይይቱ ከተሳታፊዎቹ ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ግልጽ የሆነ የፋይናንስ ስርዓት መኖር፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር ማዳብር፣ ሌሎች አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀምና ተመሳሳይ አሰራር በሁሉም የመንግስት ልማት ድርጅቶች እነዲሰፍን ከስምምነት ተደርሷል፡፡   

Average (0 Votes)