News and Updates News and Updates

የቡድን 24 ሃገራት የቴክኒክ ባለሞያዎች ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ

የቡድን 24 አባል ሀገራት የቴክኒክ ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ ዐበይት ጉዳዮች በሆኑት በመሰረተ ልማት፣ በምርታማነትንና በትራንስፎርሜሽን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ታክስ አሰባሰብን በተመለከተ ለሁለት ቀናት (20/7/2009-21/7/2009)በአዲስ አበባ ምክክር ያደርጋሉ፡፡

በጉባኤው ላይ ተገኘተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚንስትር / አብርሃም ተከሰተ እንደተናገሩት የቡድን 24 ዋንኛ ትኩረት የታዳጊ ሀገራትን የልማት ፕሮጀክቶች መደገፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ድምጻችንን የምናሰማበት ትልቁ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡ በመሰረተ ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በግብርና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ ይረዳል በማለት ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት 60 በመቶ የሚሆነው በጀት ለመሰረተ ልማት እያዋለች እንደሆነ ገለጸዋል፡፡ በተለይም ሀገሪቱ በኢነርጂ፣ በባቡር፣ በኤርፖርቶች ግንባታ፣ በአየር ትራንስፖርት እና ቴሌኮም ማስፋፋት እያደረገች ያለው ኢንቨስትመንት .. 2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው የዓለም ሀገራት ጋር ለመቀላለቀል በምታደረገው ጥረት ላይ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ገለጸዋል፡፡

 

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአለም አቀፍ ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ አበራ እንደተናገሩት የቡድን 24 ሀገራት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1971 የተመሰረተ ሲሆን የዚህ ድርጅት ዋንኛ ዓላማ ደግሞ ከአለም ባንክ እና ከአለም ገንዘብ ድርጅት ጋር ተያይዞ ታዳጊ ሀገሮች ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲችሉ በጋራ የሚመካከሩበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊ ሀገራት ከአለም ባንክም ሆነ ከአለም ገንዘብ ድርጅት ጋር ተያይዞ በገንዘብም ሆነ ተጨማሪ ሀብት ከማግኘት፣ አጀንዳቸውን በግልፅ ከማራመድ አንጻር እና የአባል ሀገራቱን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለመጀመሪያ ጊዜ ማስተናገድ የቻለች ሲሆን ቡድኑንም ለአንድ ዓመት በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካ ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው እድገት በውጭ አለም ያላትን ተቀባይነት ያሳያል ብለዋል፡፡

የቡድን 24 ሀገራት የጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ሚስ ማሪሉ ሁዪ እንደገለፁት የቡድን 24 የባለሙያዎች ጉባኤ በሶሰት አበይት አጀንዳዎች ውይይት ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው በመሰረተ ልማት ላይ ሲሆን እንዴት ፋይናንስ እንደሚደረግ፣ ለሀገሮች ያለው ጥቅም፣ ታዳጊ ሀገሮች መሰረተ ልማት ከማልማት አንጻር የሚገጥማቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው፣ እንዴትስ እየተወጡት ነው በሚሉት ጉዳዮች የባለሙያዎች ቡድን በስፋት ይመክርበታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምርታማነትና ትራንስፎርሜሽንን አስመልክቶ የሚደረግ ውይይት ሲሆን ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ትኩረት የምታደርግበት ትልቅ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ሶስተኛው ነጥብ የሀገር ውስጥ ሀብት በማሰባሰብ ነው በማለት የስብሰባውን አስፈላጊነት ገልፀዋል፡፡