Skip to Content

Resources Resources


Resources Resources

Back

የመንግስትና የግል ሽርክና የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት በኢትዮጵያ

የመንግስትና የግል ሽርክና የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን የረዥም ጊዜ የልማት ራዕይ ለማሳካት ሁለተኛውን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀርጾ በመተግበር ላይ የሚገኝ ሲሆን በዚህም መሠረት መንግሥት የአገሪቱን የመሠረተ ልማት ጉድለቶች ለሟሟላት የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦትን በማመቻቸት በኩል ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል ዕቅዱ ያመለክታል፡፡ ይህም ሆኖ በመንግሥት አቅም ብቻ የአገሪቱን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት ስለማይቻል ትኩረት የሚሰጣቸው ኘሮጀክቶች እየተለዩ በመንግስትና የግል በሽርክና ሥርዓት (Public-Private Partnership) ሊለሙና ሊቀርቡ የሚችሉበት መንገድ በጥናት ተለይቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዕቅዱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንግስትና የግል ሽርክና የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስተባበሪነት ተጀምሯል፡፡ ለማዕቀፉ ዝግጅት እንዲረዳ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ከአንድ አመት ላላነሰ ጊዜ ዝግጅት ሲደረግ የቆየ ሲሆን በዚህም ሂደት ልምድ ያላቸውን አለም አቀፍ አማካሪዎች በመቅጠር፣ የተለያዩ የአለም አገሮችን ልምዶች በመዳሰስ፣ ዋነኛ ከሚባሉ ባለብዙ-ወገን እና የመንግሥታት የልማት ተባባሪ አጋሮች የሚገኝ ድጋፍን በመጠቀም እንዲሁም በቅቅርበት በመስራት ረቂቅ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡ በመቀጠልም ረቂቅ ማዕቀፎችን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከፌደራል መንግሥት መ/ቤቶች፣ ከግል ዘርፍ ተወካይ ተቋማት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከሙያ ማህበራት ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሂዶ ማዕቀፉን ለማሻሻል የሚረዳ ግብዓት ተሰባስቧል፡፡

በመቀጠልም ማዕቀፉ ለተጨማሪ ዕይታና ግብዓት ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የተላከ ሲሆን በማስከተልም ረቂቅ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚቀርብ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚሰጥ ግብዓትና አቅጣጫን መሠረት በማድረግ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን በማከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ይደረጋል፡፡

የመንግሥትና የግል ሽርክና መንግስት ከግል ሴክተር ጋር በረዥም ጊዜ ኮንትራት አማካኝነት  በጋራ  የሚሰራበት  ስምምነት ሲሆን የግል ዘርፉ ከዚህ ቀደም በመንግስት ብቻ ሲተገበሩ በቆዩ የህዝብ አገልግሎት ተግባራት አቅርቦት ላይ እንዲሣተፍ በማስቻል የአገልግሎቶችን ተደራሽነት፣ ጥራትና ቅልጥፍና ለማሻሻል የሚያግዝ አሰራር ነው፡፡